Diplomats' Note

ክቡር የኢፌዲሪ መንግስት ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለሁለቱ ምክር ቤቶች የ5ኛው የስራ ዘመን የ2ኛው ዓመት መክፈቻ ያደረጉት ሙሉ ንግግር

In this Edition

dr-m

የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣
የተከበራችሁ መላ የአገራችን ህዝቦች፣
ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶችና ክቡራትና ክቡራን፤
ከሁሉ በማስቀደም ሁለቱ ምክር ቤቶች በ5ኛው የስራ ዘመናችሁ፣ ሁለተኛውን ዓመት ለምትጀምሩበት ለዛሬው ቀን በመብቃታችን የተሰማኝን ልባዊ ደስታ በራሴና በኢፌዴሪ መንግስት ስም ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡ በዚህም አጋጣሚ በአገራችን ልዩ ልዩ አካባቢዎች በተካሄዱ ግጭቶች በህይወትም ሆነ በአካል ለተጐዱ ወገኖቻችን፣ እንዲሁም በቅርቡ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልል የኢሬቻ ባህላዊ ስነ-ስርዓትን ለማክበር ከተሰበሰቡ ወገኖቻችን መካከል ፀረ ሰላም ኃይሎች በፈጠሩት ግርግር ህይወታቸው ላለፈ ወገኖችና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለመላው የኦሮሞና የአገራችን ህዝቦች የተሰማኝን ጥልቅ ሃዘን በራሴና በመንግስት ስም ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡
የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣
የተከበራችሁ መላ የአገራችን ህዝቦች፤
በፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ስርዓታችን ወሳኝ ሚና የሚጫወቱትን ሁለቱን ምክር ቤቶች በምንከፍትበት በዛሬው እለት፣ በብዙ መሰረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መምከር እንደሚገባን ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ያሳለፍነው ዓመት አገራችን ኢትዮጵያ በብዙ መስኮች ወደፊት የተራመደችበት እንደሆነው ሁሉ ልዩ ልዩ ችግሮች የተከሰቱበትም ነበር፡፡ በመሆኑም መልካም ጅምሮችን አጠናክረን ለማስቀጠል፣ ችግሮቻችንን ደግሞ መላ የአገራችንን ህዝቦች በሚያረካ ደረጃ ለመቅረፍ ይቻል ዘንድ እነዚህን ሁኔታዎች አንስተን በዝርዝር ልንመክርባቸው ይገባናል፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በፈጣን የለውጥ ሂደት ወደፊት ስትራመድ ቆይታለች፡፡ ለማንም ግልፅ እንደሚሆነው ለውጡ ከገጠር እስከ ከተማ፣ በሁሉም የህይወት መስክ የተካሄደ ከመሆኑም በላይ ያልዳሰሰው የህብረተሰብ ክፍልም የለም፡፡ ለውጡ በዚህ ብቻ ሳይወሰን በህብረተሰባችን ውስጥ መሰረተ ሰፊ የለውጥና የተጠቃሚነት ጥያቄዎች ለመቀስቀስ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከሰራናቸው መልካም ተግባራትም ሆነ ከተፈፀሙ ድክመቶችና ከተከሰቱ ተጨባጭ ችግሮች በመነሳት፣ ቀጣዩ ሂደት ይበልጥ ፍሬያማና የህዝባችንን መብትና ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚያረጋግጥ፣ የአገራችንን ሰላምና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚያጠናክር እንዲሆን አድርጐ መቃኘት አማራጭ የሌለው ሆኖ የሚገኝበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡ በመሆኑም ባሳለፍነው ዓመት ካጋጠሙን ትልልቅ ችግሮች በመነሳት ጉዳዮን በዝርዝር መመልከትና ቀጣዮቹን አቅጣጫዎች በትክክል መተለምና በላቀ ርብርብ ተግባራዊ ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡
ባሳለፍነው ዓመት አገራችንን ከገጠሟት ችግሮች መካከል አንዱና ትልቁ ሰፊ መልክዓ ምድርን የሸፈነው የድርቅ አደጋ ነበር፡፡ ድርቁ በዓለማችን የታየውን የተፈጥሮ መዛባት ተከትሎ የተከሰተውና በአስከፊነቱ ባለፉት 50 ዓመታት ከታዩ ድርቆች ሁሉ የከፋ ነበር፡፡ በመሆኑም በብዙ ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ለረሃብ አደጋ ተጋልጠው ነበር፡፡ የድርቁ አስከፊነት በእንስሳት ሀብታችን ላይም ከባድ የመኖና የውሃ እጥረት ችግር አስከትሎ የገጠሩ ህብረተሰባችን ህይወት በቋፍ ላይ ወድቆ ነበር፡፡
ይህ አደጋ መከሰቱን የተገነዘበው የኢፌዴሪ መንግስት፣ ችግሩን በራሳችን አገራዊ አቅም በመተማመን ልንፈታው እንደምንችልና እንደሚገባን አቅዶ ተንቀሳቅሷል፡፡ አደጋው ከአገራችን አቅም በላይ ሆኖ ቢገኝ፣ በወገኖቻችን ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለማስወገድ ይቻል ዘንድ፣ በወቅቱ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ከማሳወቅ ሳይቆጠብ፣ ችግሩን በወሳኝነት በራሳችን አቅም ለመፍታት ተንቀሳቅሷል፡፡ በዚህ መሰረት አደጋውን ለመቋቋም የሚያስችለን በጀት በመመደብ፣ በአንድ በኩል ከአገር ውስጥ ትርፍ አምራች አካባቢዎች እህል በመግዛት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በድርቅ ለተጠቁ ወገኖቻችን የሚሆን ቀለብ ለማቅረብ የሚያስችል ከዓለም ገበያ የእህል ግዥ በማካሄድ ከማንኛውም ሸቀጥና ምርት ቀድሞ እንዲጓጓዝና ለተረጅዎቹ እንዲደርስ አድርጓል፡፡ ከዚህ የተሳካ እንቅስቃሴ ጐን ለጐን ለእንስሳት መኖና ውሃ ለማቅረብ የተሳካ እንቅስቃሴ አካሂዷል፡፡ በውጤቱም ከድርቁ ጋር የተያያዘ ማንኛውም አይነት  ሰብዓዊ  ቀውስና ጉዳትን ለማስወገድ ችሏል፡፡ መንግስት በራሳችን አገራዊ አቅም በመተማመን ችግሩን ለመፍታት ያደረገው ጥረት፣ ለጋሽ አገሮች በተለመደ የትብብር መንፈስ ከሰጡት እርዳታ ጋር ተዳምሮ የድርቁ አደጋ በዜጐች ላይ ይህ ነው የሚባል ጉዳት ሳያደርስ እንድናልፍ አስችሏል፡፡ በዚህ የተፈጥሮ አደጋ ወቅት ከጎናችን ሳይለይ የእርዳታ እጁን በመዘርጋት የምናውቀው ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ፣ ዘንድሮም ላደረገልን ቀና ትብብር በራሴና በኢፌዴሪ መንግስት ስም ከልብ ላመሰግን እወዳለሁ፡፡
ባለፈው ሩብ ምእተ ዓመት ያጋጠሙንን የድርቅ አደጋዎች በመቋቋም በህዝብ ላይ ሊደርስ የሚችልን ጉዳት ስናስወግድ መቆየታችን በመላ የአገራችን ህዝቦች ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ይህን የመሰለ ውጤት ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘ ነው ሊባል አይችልም፡፡ ይህም ሆኖ የዘንድሮውን ውጤት፣ ከዚህ የተለየ የሚያደርገው በወሳኝነት በራሳችን አገራዊ አቅም በመተማመን የፈታነው መሆኑ ነው፡፡ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎች በተከናወኑባቸው ቦታዎች የከርሰ ምድር ውሃ ይዞታችን እንደበለፀገና  ለክፉ ቀን ስንቅ ሆኖ እንዳገለገለን በተጨባጭ ተረጋግጧል፡፡ በተጨማሪም ባለፈው ዓመት ያጋጠመን የምርት ቅናሽ በሌላ ጊዜ ከሚያጋጥመን ያነሰ እንደነበርም ታይቷል፡፡ በድርቅ በተጠቃንበት ዓመት ከመኸር ግብርና የተገኘው 26.7 ሚሊዮን ቶን  የግብርና ምርት ከዚያ በፊት ከነበረው በመጠኑ ተመሳሳይ መሆኑ ሲታይ የግብርና ልማት አቅጣጫችንን ትክክለኛነት በድጋሚ አረጋግጧል፡፡  ይህም አገራችን ባለፉት 25 ዓመታት የኢኮኖሚ እድገትና የፈጠረችው አገራዊ የመቋቋም አቅም፣ በድርቅ የመጠቃት አደጋ በሚያጋጥምበት ጊዜ ከማንም እርዳታ ሳንጠብቅ ችግሩን በራሳችን አቅም ለመፍታት እንደምንችል ያረጋገጠ ሆኗል፡፡ ይህ የመላ የአገራችን ህዝቦች የትግልና ልማታዊ ርብርብ ውጤት በመሆኑ መላ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ታላቅ አገራዊ ድል ልባዊ ኩራት ሊሰማን ይገባል ብየ አምናለሁ፡፡ በመሆኑም በዚሁ አጋጣሚ በዚህ መስክ የጀመርነውን መልካም ስራ ከመቸውም ጊዜ በላይ አጠናክረን ልንገፋበት እንደሚገባን ለማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡
በዘንድሮው ክረምት በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች የተመጣጠነና ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ በማግኘታችን፣ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ካለፈውም በጣም የተሻለ ምርት ሊያገኙ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡ ተጨባጭ ውጤቱ ወደፊት የሚገመገም መሆኑ እንደተጠበቀ፣ ከእንግዲህ ሊያጋጥም የሚችል ማንኛውም ዓይነት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ጉዳት እንዳያደርስ ተጠንቅቀን እስከተረባረብን ድረስ የ2008/09 የግብርና ምርታችን ከፍተኛ ጭማሪ የሚገኝበትና የህዝባችንን ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚያጐለብት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣
የተከበራችሁ መላ የአገራችን ህዝቦች፣
ባሳለፍነው ዓመት ያጋጠመንን የድርቅ አደጋ ለመቋቋም ከፍተኛ ጥረት እያደረግን በነበረበት ወቅት፣ የተከሰተው ሌላው አገራዊ ችግር፣ ሰፋ ባሉ የአገራችን አካባቢዎች ሁከትና ግጭት መቀስቀሱና አንፃራዊ የፖለቲካ አለመረጋጋት ጐልቶ መታየቱ ነበር፡፡ ለሁላችንም ግልፅ እንደሚሆነው አገራችን ለሃያ አምስት ዓመታት አስተማማኝ ሰላም ተጎናፅፋ የቆየች ቢሆንም፣ በልዩ ልዩ የአገራችን ክፍሎች፣ በተለይ ደግሞ ወጣቶች የተሳተፉባቸው ሁከቶችና ግጭቶች ተቀስቅሰዋል፡፡ በእነዚህ ግጭቶች ሳቢያ በአሳዛኝ ደረጃ የወጣቶችና ሌሎች ዜጐች፣ እንዲሁም የፀጥታ አስከባሪ ሃይሎቻችን ህይወት ተቀጥፏል፡፡ ቀላል የማይባል ንብረትም ወድሟል፡፡ በተጨማሪም የዜጐች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ተስተጓጉሏል፡፡ በዚህ የተነሳ ደፋ ቀና ብለው ሰርተው ኑሮአቸውን ለማሸነፍ የሚንቀሳቀሱ ዜጐች ለብዙ ፈተናዎች ተዳርገዋል፡፡ ይህን የመሰለው ችግር በየአካባቢው እንዲቀሰቀስ ምክንያት የሆኑ ወቅታዊ ችግሮች እንደነበሩ ባይካድም፣ ከተከሰተበት ስፋትና ከደረሰው የህይወትና የንብረት ጉዳት በመነሳት መሰረታዊ ምክንያቶቹን በውል ማስቀመጥ ይገባል፡፡ እነዚህን ለመፍታት የሚያስችል የተሟላ የመፍትሔ ሃሳብ በማዘጋጀት መላውን ህብረተሰብ በሚያሳትፍ አግባብ ተግባራዊ ማድረግ አማራጭ የሌለው ሆኖም ተገኝቷል፡፡
ለማንም ግልፅ እንደሚሆነው ባሳለፍነው ዓመት በተከሰቱት ግጭቶች ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ የነበሩት የአገራችን ወጣቶች ነበሩ፡፡ በከተማም በገጠርም በተከሰቱት አለመረጋጋቶች ሰፋ ያለ የወጣት ኃይል ቀጥተኛ ተሳታፊ ነበር፡፡ ይህ እውነታ ወጣቶቻችን የሚገኙበትን ሁኔታ በትክክል መገንዘብና ለችግራቸውና ለጥያቄያቸው የሚመጥን መሰረታዊ መፍትሔ ማቅረብ የሚሻ ሆኖ ይገኛል፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ በህዝብ ብዛት ከአፍሪካ በ2ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ወደ መቶ ሚሊዮን ከሚጠጋው ህዝቧ ውስጥ ደግሞ ከግማሽ የማያንሰው በወጣት የእድሜ ክልል የሚገኝ ነው፡፡ ስለሆነም በህብረተሰባችን ውስጥ የሚካሄድ ማንኛውም የለውጥ እንቅስቃሴ ተወደደም ተጠላም የግድ ወጣት ተኮር ባህርይ ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አብዛኛው የአገራችን ህዝብ በገጠር የሚገኝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወጣቱም በዋነኛነት ተከማችቶ የቆየውና ዛሬም የሚገኘው በዚሁ የገጠሩ ክፍላችን ነው፡፡ ፡፡ በከተሞች ቁጥሩ እየተበራከተ የመጣው የተማረውም ያልማረውም ወጣት የስራና የተጠቃሚነት እድልም ቢሆን መፍትሄ የሚሻ መሆኑ አልቀረም፡፡
የገጠሩ ወጣት ኃይል ለረጅም ጊዜ በአካባቢው ተወስኖ ከቆየ በኋላ በተወሰኑ መሰረታዊ ምክንያቶች ወደ ከተሞች በመፍለስ ላይ ይገኛል፡፡ አብዛኛው የገጠር ወጣት መሬት አልባ በመሆኑ ከገጠሩ ጋር ተጣብቆ የሚቆይበት ጠንካራ ምክንያት የለውም፡፡ በዚህ ላይ የግብርና ምርታማነት እየጨመረ መሄዱን ተከትሎ፣ በመፈጠር ላይ ያለው ትርፍ ጉልበት ገጠርን እየለቀቀ በብዛት ወደ ከተሞች እንዲንቀሳቀስ ግድ የሚልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በተጨማሪም በአገራችን የተስፋፋው የትምህርት እድል ተጠቃሚ የሆነው የገጠር ወጣት ከወላጆቹ ልማዳዊ የግብርና ስራ ውጭ ሌላ አማራጭ የሚያማትርበት ሁኔታ እየሰፋ በመምጣቱ ቀስ በቀስ ወደ ከተሞች በተለይ ደግሞ ወደገጠር ከተሞች እየተሸጋገረ በእነዚህ ውስጥ መከማቸት ጀምሯል፡፡
ይህ ወጣት ገጠሩን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የለቀቀ ቢሆንም፣ በከተሞቻችን አስተማማኝ የስራና የገቢ ሁኔታ ገና ያልተፈጠረለት ነው፡፡ በተከማቸባቸው ከተሞች ሁሉ በዋነኛነት ከእለት ስራ ያለፈ ቋሚ የስራና የገቢ እድል የሌለው በመሆኑ ህይወቱ አስተማማኝ መሰረት ያልያዘ ነው፡፡ ሁኔታዎች ዘንበል ያሉ ቀን ለከፋ አደጋ እጋለጣለሁ ብሎ በሰቀቀንና እርግጠኛነት በማጣት ውስጥ የሚገኝ ወጣት ነው፡፡ ይህን የመሰለው ወጣት በትንንሽ የገጠር ከተሞች ብቻ ሳይሆን፣ በትልልቅ ከተሞችም ጭምር የሚገኝ በመሆኑ መንግስት ከመቸውም ጊዜ የተለየ ወጣት ተኮር ርብርብ ካላደረገ በስተቀር፣ አገራችን በቅርቡ ለተከሰተው ዓይነት ፖለቲካዊ ችግር በተደጋጋሚ መጋለጧ እንደማይቀር መገንዘብ ይገባል፡፡
መንግስት የወጣቱን ችግር ለማቃለል ባለፉት ዓመታት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደተንቀሳቀሰ ይታወቃል፡፡ በተለይ ደግሞ ከ3ኛው አገራዊ ምርጫ በኋላ የወጣቶች የልማትና ተጠቃሚነት ፓኬጅ ተቀርፆ በተካሄደው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ብዙ የአገራችን ወጣቶች ተጠቃሚ መሆን እንደጀመሩም ይታመናል፡፡ ይህም ሆኖ ከዚህ ቀደም የተዘጋጀው መፍትሄም ሆነ በዚሀ ላይ በመመስረት የተከናወነው ስራ እጅግ እየሰፋ ከመጣው የወጣት ቁጥርና ፍላጐት ጋር ፈፅሞ የሚመጣጠን እንዳልሆነ ታይቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለወጣቶች ታስበው የተቀረፁ የልማትና ተጠቃሚነት ኘሮግራሞች በመንግስት በኩል በሚታዩ የተለያዩ ድክመቶች፣ በተለይ ደግሞ በአፈፃፀም ብቃት መጓደልና በስነ ምግባር ጉድለቶች ሲደነቃቀፉ  የወጣቱ ትውልድ ቅሬታ እንደሚባባስ ታይቷል፡፡ በመሆኑም ባሳለፍነው ዓመት የተከሰቱት ችግሮች በመሰረቱ ከኢኮኖሚ ፍላጐትና ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጋር የተያያዙ በመሆናቸው እነዚህን ችግሮች የራሱን የወጣቱን ትውልድ በቀጥታና ዴሞክራሲያዊ አኳኋን በሚያሳትፍ አቅጣጫ መፍታት ጊዜ የማይሰጥ ተደርጐ ሊወሰድ ይገባዋል፡፡
ባሳለፍነው ዓመት የተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት ከተጠቃሚነት አኳያ ያመጣው ችግር የአገራችንን ወጣቶች ብቻ የሚመለከት አልነበረም፡፡ በአገራችን ፈጣን ብቻ ሳይሆን መላውን ህዝብ በየደረጃው ተጠቃሚ የማድረግ ግብ ይዘን በምንገነባው ኢኮኖሚ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጥቅም በፍትሃዊነት የማስከበር ጉዳይ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ሁሌም ቢሆን ይህንኑ በፍትሃዊነት እያሳካን በመሄድ ላይ መሆናችን እየተረጋገጠ ሊሄድ የሚገባው ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ ቁጥራቸው ሰፊ የሆኑትና በደመወዝ የሚተዳደሩ ወገኖች ከሚያጋጥማቸው የኑሮ ውድነትና የቤተሰብ ኃላፊነት ጋር በተጣጣመ ደረጃ መጠቀም መጀመራቸውን ማረጋገጥ አማራጭ የሌለው ሆኗል፡፡ መንግስት በዚህ ረገድ ያነገበውን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት አላማ ለማሳካት በማለም ባለፉት በርካታ ዓመታት ድህነትን ለመቀነስ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ተንቀሳቅሷል፡፡ ከጠቅላላ አገራዊ በጀታችን ውስጥ እጅግ አብዛኛውን ድሃ ተኮርና የዜጐችን የማምረት አቅም በመገንባት ላይ ያነጣጠረ እንዲሆን ማድረጉ ተገቢ ቢሆንም በዚህ ረገድ በተለይ ከእድገታችን ጋር በተገቢው ደረጃ መጠቀም ያልጀመሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግር ለማቃለል በተለየ ትኩረት መንቀሳቀስ አጣዳፊ ሆኖ ይገኛል፡፡
ባሳለፍነው አመት አጣዳፊ መፍትሄ የሚሹ ሆነው ከታዩት ችግሮች ሌላው በከተሞች አቅራቢያ በሚገኙ ገጠሮች የሚከሰት የአርሶ አደርና የአርብቶ አደር ወገኖቻችን መፈናቀል ጉዳይ ነው፡፡ አገራችን ታዳጊ እንደ መሆኗ ከተሞቻችን በልዩ ልዩ ምክንያቶች ወርድና ቁመታቸው እየጨመረ እንደመጣና ወደፊትም ይህ ዝንባሌ እየሰፋ እንደሚሄድ ለመገመት አያስቸግርም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በገጠር ሰፋፊና ዘመናዊ እርሻዎችን እንዲሁም ትልልቅ የሃይል ማመንጫና የመስኖ ግድቦችን የመስራት ፍላጎታችንም የገጠር መሬትን ከመጠቀም ውጭ ሊሳካ የማይችል ነው፡፡ በመሆኑም ዘመናዊ እርሻዎችና ትልልቅ ግድቦች መስፋፋታቸው ቀጣይ በመሆኑ ይህን ከአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ መብትና ጥቅም ጋር በተጣጠመ አኳኋን መፈፀም አማራጭ የሌለው ሆኖ ይገኛል፡፡  አርሶ አደሩ የተቻለውን ያህል መሬቱን ከፍተኛ ጥቅም ሊያገኝ በሚችልበት ሁኔታ እንዲያለማው ከማድረግ ጀምሮ፣ ለላቀ አገራዊ ጥቅም በሚፈለግበት ጊዜ ደግሞ፣ ይህንኑ ከአርሶ አደሩና ከአርብቶ አደሩ ዘላቂ፣ ቀጣይና ታዳጊ ተጠቃሚነት በማይነጠል መልኩ ልንፈፅመው የሚገባን ሆኖ ይገኛል፡፡  ሃቁ ይህ ቢሆንም በከተሞች አቅራቢያ የሚካሄደውም ሆነ፣ በሌሎች አካባቢዎች የአርሶ አደርና አርብቶ አደር መፈናቀል ከተመጣጣኝ ካሳና የማቋቋም እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ሲፈፀም እንዳልቆየ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ በዚህ የተነሳ በተለይ ለከተሞች በቀረቡ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮቻችን ለልዩ ልዩ ቅሬታዎች ሲጋለጡ ቆይተዋል፡፡  በመሆኑም በያዝነው አመት ይህን ችግር ለመቅረፍ የማያስችል አቅጣጫ ይዘን በመረባረብ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ለማስፋት ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ካላግባብ የመጠቀም አዝማሚያ የተጠናወታቸው ጥቂት ማህበራዊ ኃይሎች ለአገራዊ እድገት ካበረከቱት አስተዋፅኦ በላይ ሲጠቀሙ የሚታዩ በመሆኑ የፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ጉዳይ በጥብቅ መፈተሽና ማስተካከል አስፈላጊ ሆኖ ይገኛል፡፡ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች አገራችን በከፈተችው እድል ከመጠቀም ወደኋላ የማይሉ ቢሆኑም፣ የመንግስትን ህግ አክብሮ በመንቀሳቀስም ሆነ የግብር ግዴታቸውን በመወጣት ደረጃ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንደማይወጡ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ለአገራዊ እድገት ካበረከቱት አስተዋፅኦ በላይ የሚጠቀሙ ክፍሎች የሚራመዱበትን የህገ ወጥ ተጠቃሚነት አቅጣጫ በመከላከልና በመቆጣጠር፣ ከዚህም አልፎ የግብር መክፈልና ህግ የማክበር ግዴታቸውን እንዲወጡ በማስገደድ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ የማያጠራጥር ተፈፃሚነት እንዲኖረው ማድረግ ይገባል፡፡
በዚህ አጋጣሚ በቅርቡ በአንዳንድ የአገራችን ክልሎች ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በኃይል ለመናድ ሲካሄዱ የቆዩ አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን መሰረታዊ ባህርይና እንድምታ በትክክል መገንዘብ ተገቢ ሆኖ ይገኛል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በህብረተሳባችን ዘንድ በተለይ ደግሞ በወጣቶቻችን በኩል የተነሱ ፍትሃዊ ጥያቄዎችን ተገን በማድረግ አንዳንድ አፍራሽ ኃይሎች ቅሬታን ወደሁከትና አውዳሚ እንቅስቃሴ ለመቀየር ተረባርበዋል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት ከኖረችበት ማሽቆልቆል ወጥታ በእድገት ጎዳና መገስገስ በጀመረችበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት በትንሳኤ ላይ መሆናችንን የማይቀበሉ አገሮችና የኒዮ ሊበራል አጀንዳቸውን ሊጭኑብን የተዘጋጁ ኃይሎች፣ ወደትርምስ እንድንገባ አቅደው፣ አገራችንን ለማተራመስ በስፋት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ይፋ ሆኗል፡፡ በተለይ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የማንንም እጅ ሳንጠብቅ በመላ የአገራችን ህዝቦች ተሳትፎና በአገራዊ አቅማችን በመተማመን መገንባት መጀመራችን ያስቆጣቸው አገሮች፣ ረዘም ላሉ ዓመታት ውስጥ ውስጡን ሲዘጋጁ ከርመው በአሁኑ ጊዜ ፅንፈኛ የዳያስፖራ ኃይሎች ከቀሰቀሱት ነውጥ ጋር በመመጋገብ  አገራችንን ለማተራመስ በቀጥታ እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡ በቀላሉ ሊያነሳሱዋቸው የሚችሉ ወጣቶችን የጥፋት ሃሳቦች፣ እንዲሁም ክብሪትና ነዳጅ እያስታጠቁ ለአገራችን ቁልፍ ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ ያላቸውን ፋብሪካዎች፣ የአበባ እርሻዎችና ሌሎች ተቋማት በማጋየት ከፍተኛ ውድመት አስከትለዋል፡፡ የግለሰቦችን ቤቶችና ሌሎች ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች አውድመዋል፡፡ ይህን ድርጊት መንግስት ለቴክኖሎጅ ሽግግርና አገራዊ ልማትን ለማፋጠን በማሰብ ያስፋፋውን ዘመናዊ የመገናኛ መሰረተ ልማት ለክፋትና ውድመት በመጠቀም  ያስተባበሩት ደግሞ አገራችን በአሸባሪነት የሰየመቻቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ናቸው፡፡ የኦነግና ግንቦት ሰባት መሪዎች ከግብፅ መንግስት ተቋማት ጋር እጅና ጓንት በመሆን ባቀናበሩት የጥፋት እንቅስቃሴ በርካታ አገራዊና የውጭ ባለሃብቶችና ሰራተኞቻቸውን ለአደጋ ያጋለጠ የታሰበበት ከፍተኛ ውድመት ፈፅመዋል፡፡  ይህ ከአገራችን ወጣቶች ፍትሃዊ ጥያቄዎች ጋር አንዳችም ተዛምዶ የለውም፡፡
ከፅንፈኛ ዳያስፖራዎች ጀምሮ በአባይ ወንዛችን ላይ የተጠቃሚነት መብታችንን ለማረጋገጥ የጀመርነውን እንቅስቃሴ ለማኮላሸት የሚንቀሳቀሱት እነዚህ ወገኖች፣ በቅርቡ ታላቁን የእሬቻ በዓል ከማወክ ጀምሮ በልዩ ልዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ያካሄዱት ውድመትና ቃጠሎ በማንኛውም ሚዛን ፍትሃዊነት የሌለው ነው፡፡ በመሆኑም መንግስት ይህን የመሰለው አፍራሽና ከባድ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ታዝሎ የመጣ ፀረ-ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ እንዲመከትና ወንጀለኞቹም በጥብቅ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ በቃጠሎ የወደሙ ንብረቶች በተለይ ደግሞ የምርት ተቋማት አገራችንና ህዝቦቿ ከውጭ የልማት አጋሮቻችን ጋር በመተባበር በአፋጣኝ መልሰው እንዲገነቡና ለላቀ ምርታማነት እንዲበቁ ጠንካራ ርብርብ ይደረጋል፡፡ በመሆኑም መላ የአገራችን ህዝቦች ኢትዮጵያን እንደፈራረሱት የሰሜን አፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ለማተራመስ የሚደረገውን ይህን አፍራሽና አሳፋሪ ሙከራ መንግስትና ህዝብ በጀመሩት መንገድ በጋራ ይፋለሙታል፡፡
የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣
የተከበራችሁ መላ የአገራችን ህዝቦች፣
2ኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባራዊ ማድረግ በጀመርንበት ዓመት የተከሰቱት ችግሮች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንድምታ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታችንን በማዳበር ልንፈታቸው የሚገባ ልዩ ልዩ ፖለቲካዊ ችግሮች እንዳሉም አመላክተውናል፡፡ በዚህ ረገድ ቀዳሚው ጉዳይ በአገራችን የብሔር ብሔረሰቦችን መብት መሰረት አድርገው የሚነሱ የማንነት ጥያቄዎችን በህገ-መንግስታችን በጥብቅ በመመራት የመፍታት አስፈላጊነት ነው፡፡ ለማንም ግልፅ እንደሚሆነው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን የተዋቀረው አገራችን የብዙ ህዝቦች አገር የመሆኗን እውነታ ያለማቅማማት በመቀበል ነው፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ የአንድ ቋንቋ፣ ወይም ባህል አገር ሳትሆን፣ የብዙ ቋንቋዎችና ሌሎች የማንነት መገለጫዎች ባለቤት የሆኑ ብዙ ህዝቦች እናት አገር ነች፡፡ ቀደም ሲል በአገራችን ይህን እውነታ በመካድ ብሔር ብሔረሰቦቻችን ካላግባብ የተያዙበት መንገድ ለግጭትና ለዘመናት የእርስ በእርስ  ጦርነት መንስዔ እንደነበር በመገንዘብ፣ አዲሱ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ብዝሃነትን በማወቅና በመቀበል እንዲሁም በአግባቡ በማስተዳደር ላይ እንዲመሰረት ተደርጓል፡፡ ይህም በመሆኑ አገራችን ለ25 ዓመታት የዘለቀ አስተማማኝ ሰላም ተጐናፅፋ ቆይታለች፡፡
ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የተገነባው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የአብዛኞቹን ብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ በተግባር የመለሰ ቢሆንም፣ በተወሰነ ደረጃ መሰረተ ሃሳቡ ተግባራዊ ያልተደረገባቸው ማህበረሰቦች ደግሞ እንደነበሩ ታይቷል፡፡ በዚህ የተነሳ ዘግይተው ጥያቄ የሚያቀርቡ ራሳቸውን የቻሉ ማህበረሰቦች የተከሰቱ ሲሆን፣ የነዚህ ህዝቦች ጥያቄ በዴሞክራሲያዊው ህገ መንግስታችን ማዕቀፍ ሊስተናገድ የሚችልና የሚገባው ሆኖ ይገኛል፡፡ ይሁንና ይህን የመሰለው ፍትሃዊ ጥያቄ  በወቅቱ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ ባለመደረጉ በተለያዩ አካባቢዎች ለግጭት መንስኤ ሲሆን ታይቷል፡፡ ይህም ሆኖ ግጭቱ የተቀሰቀሰው አንዳንድ ወገኖች እንደሚያስቡት ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአታችን ለግጭት መንስዔ ስለሆነ፣ ወይም ደግሞ በማንነት ዙሪያ የሚነሱ አዳዲስ ጥያቄዎችን በብቃት ለማስተናገድ የሚቸገር በመሆኑ አይደለም፡፡ ፌዴራላዊ ስርአታችን በመሰረታዊ ባህሪው የማህበረሰቦችን ማንነት የሚያከብር በመሆኑ ችግር ፈች እንጅ ችግር ፈጣሪ ወይም አባባሽ አይደለም፡፡ ይህ ሩቅ ሳንሄድ አዲሱ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት፣ አገራችን በዘመናዊ ታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ሩብ ምዕተ ዓመት የሞላው ረዥም የሰላም ዘመን እንድትኖር፣ ህዝቦቿ ለሃያ አምስት ዓመታት በሰላም፣ በፍቅርና በመካባበር እንዲኖሩ ያስቻለን በመሆኑ የሚረጋገጥ ነው፡፡ ስለሆነም  ችግሩ በተጨባጭ የተነሳው ከስርአቱ ባህሪ ሳይሆን፣ ማህበረሰቦች የሚያነሱትን የማንነት ይከበርልን ጥያቄ ከህገ-መንግስታዊው ድንጋጌ በመነሳትና ይህንኑ በጥብቅ በማክበር መመለስ ሲገባ ከዚሁ ተቃራኒ በሆነ አያያዝ በአንዳንድ አካባቢዎች በመፈፀሙ ነው፡፡
ከዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አኳያ ሌላው ትኩረት የሚሻ ሆኖ የተገኘው ራሱን ዴሞክራሲያችንን ከእድገታችን ጋር በተገናዘበ ሁኔታ ተግባራዊ የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡ አገራችን ባፀደቀችውና በምትመራበት ህገ-መንግስት ዴሞክራሲያዊ የአስተዳደር ስርዓትን መርጣለች፡፡ የመረጥነው ዴሞክራሲያዊ  ስርዓት ለአንዴና ለሁልጊዜ ረግቶ የሚቀመጥ ሳይሆን፣ ከአገሪቱ የእድገት ደረጃ ጋር ተገናዝቦ ሁሌም ቢሆን በታዳጊነት መገንባትና እየዳበረ መጓዝ ያለበት ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት በአገራችን ብዝሃነት ያሉዋቸው ማህበረሰቦች እንደሚገኙና እነዚህም የየራሳቸው ልዩ ልዩ ፍላጐቶች ያሏቸው መሆኑን በመገንዘብ የተለያዩ ጥቅሞችን በማቻቻልና በማጣጣም ልትመራ የሚገባት እንደሆነ ታምኖበት በዚሁ ቅኝት ስትራመድ ቆይታለች፡፡ ከሁሉ በፊት በጥቅሞች መካከል የሚከሰቱ ልዩነቶች ሁሉ በዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ መንገድ እንዲገለፁ ማድረግ፣ አገራችን በተረጋጋ መንገድ ለመቀጠል እንድትችል የሚያደርጋት ቁልፍ እንደሆነ ታምኖበት ፍላጐቶች በነፃነት እንዲገለፁ ሲደረግ ቆይቷል፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከመልካም አስተዳደር ችግርና ከመሳሰሉት ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ቅሬታዎችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከማስተናገድ አኳያ በመንግስትም ሆነ በህብረተሰብ ደረጃ ጉልህ ክፍተቶች እንዳሉ ተስተውሏል፡፡ በመንግስት በኩል ለህዝብ ቅሬታ መባባስ ምክንያት የሆኑ ችግሮችን በፍጥነት ካለማረም ጀምሮ ህዝብ የተሰማውን ቅሬታ በዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ መልክ ይገልፅ ዘንድ በበቂ ሁኔታ ያለማስተናገድ ችግር ታይቷል፡፡ በአንዳንድ የህብረተሰቡ ክፍሎች በኩል ደግሞ፣ ህገ-መንግስታዊ ስርዓታችን ማንኛውንም ጥያቄ ሆነ የህዝብን ፍላጐት በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለማራመድ የሚያስችል ብቁ የመታገያ ማዕቀፍ እንዳጎናፀፈን  በውል ባለመገንዘብ፣ በጥቂቱም ቢሆን ከህገ መንግስታዊ ስርአቱ ውጭ በሚታዩ ሁከቶች በመሳተፍ መልክ የሚታዩ ስህተቶች ተስተውለዋል፡፡ አልፎ አልፎ በተለይ ደግሞ በወጣቶቻችን ዘንድ  ህግ በመጣስ መንግስትና ህዝብን ለማጋጨት የሚሹ አፍራሽ ሃይሎችን በየዋህነት በመከተል የተሳሳቱ የትግል ስልቶች የመጠቀም አዝማሚያ ታይቷል፡፡ በዚህ ረገድ ፍላጐትን በሰላማዊ ሰልፍ አማካይነት ከመግለፅ መብት ጋር ተያይዘው የተከሰቱ ችግሮችን ማስታወስ ይቻላል፡፡ እነዚህ ችግሮች በመንግስትም ሆነ በህብረተሰብ ደረጃ ዴሞክራሲያችንን በማበልፀግ ተጨማሪ እርምጃዎች መራመድ እንዳለብን የሚያመላክቱ ሆነዋል፡፡
ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችንን ከማበልፀግ አኳያ ሌላው ትኩረት የሚሻው ጉዳይ በአገራችን የፍላጐት ብዙህነት እንዳለ ተገንዝቦ፣ እነዚህን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመግለፅ የሚቻልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ከማድረግ አኳያ የምክር ቤቶቻችንን ተዋፅኦ የማጐልበት ጉዳይ ነው፡፡ እንደሚታወቀው አገራችን በምትከተለው የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ስርዓት በመመራት ባለፉት ሀያ አምስት ዓመታት በድምሩ  ለአስር ጊዜ አገራዊ፣ ክልላዊና ከባቢያዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡ በእነዚህ ምርጫዎች የብዙ ፓርቲዎች ተሳትፎ የነበረ ሲሆን፣ በተለይ ባለፉት ሁለት ምርጫዎች እንደተከሰተው በምክር ቤቶቻችን የገዥው ፓርቲ ሙሉ የበላይነት ያለበት ሁኔታ ተስተውሏል፡፡ ይህ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተካሄደ ምርጫ  የህዝብ ድምፅ ያስገኘው ውጤት እንደሆነ ባያጠያይቅም፣ በአገራችን ወሳኙ የስልጣን አካል በሆነው ምክር ቤት የማይወከሉ ድምፆች እንዲኖሩ አድርጓል፡፡ በመሆኑም ከገዥው ፓርቲ በተለዩ ፓርቲዎች የሚወከል ጥቅምና ፍላጐት ያላቸው ማህበረሰቦችን የሚወክሉ ፓርቲዎች በምክር ቤቶቻችን ውስጥ የመሳተፍ እድል ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡ ስለሆነም ይህን የመሰለው ሁኔታ ስርዓታችን ተረጋግቶ እንዲቀጥል ከማድረግ አኳያ የራሱ አሉታዊ ተፅእኖ የሚያስከትል በመሆኑ፣ በተቻለ መጠን ከቀጣዩ ምርጫ በፊት ዴሞክራሲያዊ መድረኮችን በማስፋትና በቀጣዩ ምርጫም በህግ ማእቀፍ በተደገፈ አኳኋን የህዝብ ምክር ቤቶች የተለያዩ ድምፆች የሚሰማባቸውና የሚፎካከሩባቸው መድረኮች እንዲሆኑ በማድረግ ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡
የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታችን ለፓርቲዎች ተሳትፎ ከሚሰጠው ትኩረት ባልተናነሰ ደረጃ፣ በከፍተኛ ትምህርትና በልዩ ልዩ የስራ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ምሁራንን ጨምሮ በተለያዩ የሲቪክ ማህበረሰብ አደረጃጀቶች ውስጥ የሚተፉ ዜጎችን በቀጥታ በማሳተፍ ጠቃሚ ሃሳቦቻቸውን ሁሉ ለአገር ግንባታ ማዋል ይጠይቃል፡፡ በዚህ ረገድ ልዩ ልዩ መድረኮችን በመክፈት የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ለማረጋገጥ የተለያዩ ጅምር ጥረቶች እንዳሉ ባያጠያይቅም እስካሁን የተደረጉት ጥረቶች በቂ እንዳልሆኑ ለመገንዘብ አያስቸግርም፡፡ በተከፈቱት መድረኮች የሚቀርቡ አስተያየቶችን በውል አዳምጦ ጠቃሚዎቹን ያለማቅማማት በመውሰድ፣ የተሳሳቱና ጐጅ አስተያየቶችን ደግሞ በአመክንዮና ጭብጦች ታግዞ በማስተካከል፣ የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎና አስተዋፅኦ ወደሚገባው ደረጃ ማድረስ አስፈላጊ ሆኖ የሚገኘው ከዚህ የተነሳ ነው፡፡
በአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን በታዳጊ አኳኋን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ ትኩረት የሚሻ እንደሆነ የተረጋገጠው ሌላው ጉዳይ በስነ ምግባርና ስነ ዜጋ እሴቶች የታነፀ ትውልድ የመፍጠር ጉዳይ ነው፡፡ በየትኛውም ዓለም ዜጐች መብትና ግዴታቸውን በውል ተገንዝበው፣ ከእያንዳንዳቸው የሚጠበቀውን ኃላፊነት እየተወጡ፣ በመብቶቻቸው ላይ ደግሞ የማይደራደሩ ሆነው እስከተገነቡ ድረስ አገሮች በእድገት ጐዳና እንደሚራመዱ ይታወቃል፡፡ በእኛም አገር ከዚህ የተለየ ሊሆን አይችልም፡፡ ዜጐች በአገር ግንባታ ሂደት ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ ትምህርትና ክህሎትን ማስፋፋት አማራጭ የሌለው ቢሆንም፣ ከዚሁ በማይነጠል መልኩ በስነ ምግባርና ስነ ዜጋ እሴቶች የታነፀ ትውልድ የመፍጠር ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ሆኖ ይገኛል፡፡
የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣
የተከበራችሁ መላ የአገራችን ህዝቦች፣
ከወቅታዊ የአገራችን ሁኔታ በመነሳት እነዚህን የመሳሰሉ ጉዳዮች አጣዳፊ መፍትሔ የሚሹ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ዛሬም እንደ ትላንቱ አገራችንን በታለመው ፈጣን የእድገት አቅጣጫ ለማስቀጠልና የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማጐልበት ሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ተግባራዊ የማድረግ ጉዳይ ልዩ ትኩረት የሚሻ ሆኖ ይገኛል፡፡ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዳችን የተሳካ አፈፃፀም በመበረታታት የነደፍነው ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ወደ ተግባር ከተሸጋገረ አንድ ዓመት አስቆጥሯል፡፡ በዚህ መሰረት ባሳለፍነው ዓመት በሁሉም መስኮች እቅዳችንን ተግባራዊ ለማድረግ የተንቀሳቀስን ቢሆንም፣ አፈፃፀማችን በልዩ ልዩ ተግዳሮቶች ተፅዕኖ ስር ለማለፍ የተገደደ እንደነበር ከመላ የአገራችን ህዝቦች የተሰወረ አይደለም፡፡ ድርቁና ከሞላ ጐደል አብዛኛውን የዓመቱን ክፍል የሸፈኑ የፖለቲካ ችግሮች በአፈፃፀማችን ላይ ራሳቸውን የቻሉ ተፅእኖዎች ያሳደሩ ነበሩ፡፡ ምንም እንኳ በትልልቆቹ ኘሮጀክቶቻችን አፈፃፀምና የተሻለ ዝናብ ከመገኘቱ ጋር ተያይዞ በታየው የተሻለ የግብርና ምርታማነት ኢኮኖሚያችን አሁንም በእድገት ጐዳና መቀጠሉ እንደማይቀር ብናምንም፣ አገራችን ከፈጠረችው መልካም መነሻና ካላት ድልብ አቅም በመነሳት ለላቀ ውጤት ተግተን መስራት የሚገባን ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ባሳለፍነው ዓመት ያጋጠሙ ችግሮች በአፈፃጸማችን ላይ ያሳደሩትን ከባድ ተፅዕኖ በመቋቋም ሳንወሰን በዚህ ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት በሚያካክስ ደረጃ ለውጥ ለማምጣት መረባረብ ያስፈልጋል፡፡
ከዚህ በመነሳት በያዝነው ዓመት የግብርና ኘሮግራማችን በተለምዶ ጥሩ እድገት ሲያሳዩ የቆዩትን የግብርና መስኮች ለላቀ ውጤታማነት ለማብቃት እንቀሳቀሳለን፡፡ ከግብርና ዘርፉ ውስጥ በቀላሉ ከፍተኛ መሻሻል ልናሳይ የምንችለው አሁንም በተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤና በሰብል ምርት በመሆኑ እነዚህን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ አልመን መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡ የተፈጥሮ ሃብት ልማት አገራችን ያላትን እምቅ የግብርና አቅም አሟጠን እንድንጠቀምበት የሚያስችለን ዋናው መግቢያ በመሆኑ አካባቢውን ተግቶ የመለወጥ ባህል ማዳበር በጀመረው አርሶ አደርና አርብቶ አደሮቻችን እንዲሁም በየገጠሩ ወጥተው ወርደው ህዝብን በሚያስተምሩ ሙያተኞቻችን በመተማመን የመሬታችንን ለምነትና የውሃ ሃብታችንን ለማበልፀግ መረባረብ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ይደረጋል፡፡ በምንገኝበት የእድገት ደረጃ የሰብል ምርት የህልውናችን መሰረት በመሆኑና በዚህ መስክ የምናስመዘግበው እድገት ሁሉ በገጠርም ሆነ በከተማ የህዝባችንን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ቁልፍ ተፈላጊነት ያለው እንደሆነ በመገንዘብ ይህን ለማልማት መላ አቅማችንን እናረባርባለን፡፡
እነዚህ እንደተጠበቁ ሆነው የአገራችንን አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ከፍተኛ ዋጋ ወደሚያስገኙ ምርቶች ለማሸጋገር ተፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ የማሟላት ጉዳይ በእቅዱ መሰረት ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡ ከፍተኛ ዋጋ ከሚያስገኙ የግብርና ምርቶች መካከል በአነስተኛው አርሶ አደር ማሳ የሚለሙ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች፣ ደኖችና የእንስሳት ሃብታችን ልማት ዋናዎቹ ሲሆኑ፣ በዚህ ረገድ አገራችን ያላትን ድልብ አቅም በአፋጣኝና በብቁ ዝግጅት ወደማልማት እንሸጋገራለን፡፡ ከዚህ በመነሳት የግብርና ልማታችን በአንድ በኩል በቀላሉ ከፍተኛ የእሴት ጭማሪ ልናመጣባቸው በሚገባን መስኮች መረባረብን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የቀጣዩ የግብርና ዘርፍ እድገት አምጭ መስኮችን ለይቶ በበቂ ቅድመ ዝግጅት ወደማልማት መሸጋገርን በታሳቢነት የሚወስድ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ በገጠር ከግብርና ልማታችን ጋር በማያያዝ ሊመጣ ከሚገባው እድገት፣ ዋናው ተጠቃሚ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ በተጨማሪም የእነዚህ ወገኖች የመሬት ተጠቃሚነት ዋስትና ይበልጥ አስተማማኝ እንዲሆን ከማድረግ ጀምሮ፣ ለምርታቸው ተገቢውን ዋጋ አግኝተው ተጠቃሚነታቸው እንዲሰፋ የማድረግ ጉዳይ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል፡፡ በተለይ ደግሞ አይቀሬ ከሆነው የከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ፣ የገጠር መሬትን ለላቀ ጥቅም ለማዋል የሚደረግ እንቅስቃሴ የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን መሰረታዊና ታዳጊ ጥቅሞች አሳልፎ በማይሰጥ መንገድ እንደሚፈፀም ይረጋገጣል፡፡ በዚህ ረገድ ክፍተት ያለባቸውን ነባር ህጎችና አሰራሮች በማስተካከል፣ በአፈፃፀም የሚታዩ ስህተቶችን ታግሎ በማረም፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም አዳዲስ የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀትና ከሁሉ በላይ ደግሞ ተፈናቃይ አርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን በሚያሳትፍ አኳኋን እንዲፈፀም ይደረጋል፡፡
አገራችንን በግብርናው ዘርፍ ለማሳደግ የሚካሄደው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ወደ ኢንዱስትሪ መር ልማት ለመሸጋገር ዝግጅት የምናደርግበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ መሰረት ከወዲሁ ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ኘሮጀክቶች ተቀርፀው ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ሲሆን፣ በዚህ ረገድ በዋና ዋና ማዕከላት ላይ የሚነቡ ትልልቅ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በመካሄድ ላይ ነው፡፡ በሌላ በኩል የግብርና ምርቶቻችንን ባለቀለት መልኩ ለማዘጋጀት የሚያግዙ ኢንዱስትሪያዊ ተቋማት የሚስፋፉባቸው በርካታ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት በመካሄድ ላይ ነው፡፡ እነዚህ ፓርኮች በአግባቡና በትክክል እስከተመሩና በተለይ ደግሞ የአገራችን ባለሃብቶች አቅም መገንቢያ ሆነው እስካገለገሉ ድረስ፣ እሴት ከመፍጠር ፋይዳቸው ባሻገር የግሎባላይዜሽንን ማእከል ለመቋቋም የሚያስችሉን መወዳደሪያ አቅሞች የምንፈጥርባቸው እንደሚሆኑ ይታመናል፡፡
ከዚህ በመነሳት በኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ፖሊሲያችን የሚገዛና የሚመራ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት በተጠናከረ አኳኋን መከናወኑን ማረጋገጥ ተገቢ ይሆናል፡፡ አገራዊ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን ውስጥ በበቂው እንዲሳተፉ ከማድረግ በማይተናነስ አኳኋን፣ በእነዚህ መስኮች የሚሰማሩ የውጭ ባለሃብቶችም ለአገራዊ ልማት ስትራተጄያችን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበትን ሁኔታ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ደግሞ ፓርኮቹ እጅግ የምንጓጓለትን የቴክኖሎጅ ሽግግር ለማስፈፀም ቁልፍ አስቻይ መድረኮች መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባናል፡፡
የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣
የተከበራችሁ መላ የአገራችን ህዝቦች፣
ባሳለፍነው ዓመት ከተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ ጋር በማያያዝ አስፈላጊነቱ እጅግ ጐልቶ የመጣው የልማት አውድማ በገጠር የኢንዱስትሪ ልማትን የማስፋፋት ጉዳይ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት ጠቃሚና አስፈላጊ ቢሆንም፣ በገጠር የሚገኘውን ሰፊ የወጣት ሃይል አቅም ለመጠቀምም ሆነ በቀላሉ ኢንዱስትሪያዊ ግብዓት አድርገን ልንጠቀምበት የምንችለውን ሰፊ የተፈጥሮ ሃብት ከማልማት አኳያ የገጠር ኢንዱስትሪን የሚያክል የለም፡፡ የገጠር ኢንዱስትሪ በኮንስትራክሽንና በአግሮ ኘሮሰሲንግ መስኮች ከፍተኛ እሴት የመጨመር ፋይዳ ያለው እንደሆነ በፍጥነት እያደጉ ካሉ አገሮች ታሪክ በመነሳት ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ በተለይ ደግሞ የገጠር ኢንዱስትሪን የአገራችን ወጣቶች በሰፊው የስራና የሃብት ፈጠራ እድልነት እንዲጠቀሙበት ማድረግ ከተቻለ፣ በርግጥም ዘርፉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርጉም ያለው እድገትና የህዝብ ተጠቃሚነት ልናረጋግጥ የምንችልበት ነው፡፡ በመሆኑም በአገራችን ኢንዱስትሪያዊ ልማትን በማፋጠን ልናመጣው የምንፈልገውን ሽግግር አስተማማኝ ለማድረግ እንችል ዘንድ፣ ለገጠር ኢንዱስትሪ ልማት የተለየ ትኩረት እንዲሰጠው ይደረጋል፡፡
ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዳችን በመሰረተ ልማት አውታሮች ግንባታ ልዩ ትኩረት መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ አገልግሎቱን ለማስፋፋት ከሜጋ ኘሮጀክቶች ጀምሮ ከባቢያዊ ፋይዳ እስካላቸው አነስተኛ ልዩ ልዩ የመሰረተ ልማት ኘሮጀክቶች ታቅደው ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ አንጻር ሲታይ አገራችን የእድገት ደረጃ ላይ ከሚገኝ ከየትኛውም በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ካለ ሀገር በላቀ ደረጃ የመሰረተ ልማት ግንባታ በማከናወን ላይ ትገኛለች፡፡ በአገራችን በመካሄድ ላይ ያለው የመሰረተ ልማት ግንባታ በተለይ ትልልቆቹ ኘሮጀክቶች ከፍተኛ የገንዘብ ወጭ የሚጠይቁና እስኪጠናቀቁ ድረስም ረዥም ጊዜ የሚወስዱ ናቸው፡፡ በዚህ ዙሪያ መንግስት ለእድገታችን አማራጭ የሌላቸውን እንደታላቁ የህዳሴ ግድብና የባቡር ልማት የመሳሰሉ ኘሮጀክቶች በላቀ ቁርጠኝነት የሚቀጥልባቸው ይሆናል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ያለንን ውሱን አገራዊ ፋይናንስ በሰፊ ኢንዱስትሪያዊና የዘመናዊ ግብርና ሴክተር ላይ የተሰማራ አገራዊ ባለሃብት በተለይ ደግሞ ወጣት ባለሃብት ለመፍጠር በሚያስችለን አቅጣጫ ማሰማራት አጣዳፊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ከዚህ በመነሳት በመሰረተ ልማት ስራዎቻችንና እሴት የመጨመር ቀጥተኛ ፋይዳ ባላቸው ሴክተሮች መካከል የሚኖረውን የኢንቨስትመንት ፋይናንስ ስምሪት ሚዛን እያስተካከሉ መሄድ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል፡፡ በተጨማሪም በመንግስት ኘሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ የሚታየውን መጓተትና ብክነት ለመቆጣጠር ከመቸውም ጊዜ የተለየ ትኩረት እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ስራ ተቋራጮች ጥራት ያለው ስራ ማከናወናቸውን ከማረጋገጥ ጀምሮ በኮንትራት አስተዳደር ዙሪያ ከውስጥም ከውጭም የሚታዩ ብልሽቶችን በከባድ የህግ ተጠያቂነት ጭምር በማስተካከል በኘሮጀክቶች ዙሪያ የሚታየውን ብልሽት ለመቆጣጠር ትኩረት ይሰጣል፡፡
የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣
የተከበራችሁ መላ የአገራችን ህዝቦች፣
ከፍ ሲል ከተዘረዘሩት የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ማሳያ ጉዳዮች በመነሳት በያዝነው ዓመት ለየት ያለ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ስራዎችን በአጭሩ ማመላከት ተገቢ ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ ከሁሉ በፊት ትኩረት የሚሰጠው የወጣቶችን ችግር ለመቅረፍ ይሆናል፡፡ የአገራችን ወጣቶች የወደፊቷ ኢትዮጵያ ገንቢዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ዛሬ በምንገኝበት ወቅት የራሳቸው ፍትሃዊ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ፍላጐትና ጥያቄዎች ያሏቸው በመሆኑ እነዚህን በአግባቡ የመመለስ ጉዳይ ቀዳሚ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል፡፡ ከወጣቶች ጥያቄዎች መካከል ሁሉንም ችግሮቻቸውን አስተሳስሮ የመፍታት እድል የሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ጉዳይ በመሆኑ ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ወጣቶች የስራና የሃብት ፈጠራ እድላቸው በተጨባጭ እውን እንዲሆንና እየሰፋም እንዲሄድ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል፡፡ ይህ ጥረት ይሳካ ዘንድ የፋይናንስ አቅርቦትን ማስፋት፣ አዳዲስ የኘሮጀክት ሃሳቦችን ማመንጨትና አሳታፊ የአፈፃፀም ስርዓት መገንባትን የግድ ይላል፡፡
በዚህ መሰረት፣ መንግስት በያዝነው ዓመት በሁሉም ወረዳዎች የሚገኙ ወጣቶችን ለኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚነት የማብቃት ዓላማ ያለውና ለዚህ ዓላማ ብቻ የሚውል የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ በማቋቋም ስራውን ይጀምራል፡፡ ለዚህም ሲባል ለፈንዱ ማቋቋሚያ አሥር ቢሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን የወጣቶችን ተሳትፎና ቁጥጥር በሚያረጋግጥ ተዘዋዋሪ አኳኋን ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል፡፡ ለወጣቶች የስራ መነሻ ይሆን ዘንድ ከተመደበው ፈንድ ጐን ለጐን የስራ ፈጠራው የሚያተኩርባቸው መስኮች ተለይተውና ከወጣቶች ጋር ተመክሮባቸው መግባባት ላይ እንዲደረስባቸው ይደረጋል፡፡ መንግስት የወጣቶች ፈንድ አጠቃቀምና የኘሮጀክቶች ትግበራ መሰረተ ሃሳቦችን ከወረዳ አመራርና ከወጣቶች ጋር በመመካከርና ተፈላጊውን የአቅም ግንባታ ድጋፍ በመስጠት የሚያስፈፅም ሲሆን፣ የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቀየሰው ኘሮግራም በየጊዜው እየተገመገመ አስፈላጊው የማስተካከያ እርምጃ የሚወሰድበት እንዲሆን ይደረጋል፡፡
ልክ እንደወጣቶች ሁሉ የሲቪል ሰርቪሱን ጨምሮ ሌሎች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ተጨማሪ እርምጃዎችም ይወሰዳሉ፡፡ የአገራችን ሲቪል ሰርቪስ ከእድገታችን ጋር ተመጋጋቢ በሆነ ደረጃ ተጠቃሚ እየሆነ እንዲሄድ ለማድረግ በየወቅቱ የዋጋ ግሽበትን ታሳቢ ያደረገ የደመወዝ ማስተካከያ ይደረጋል፡፡
ከፍ ሲል ከተገለፁት የህዝብን ተጠቃሚነት በተለይ ደግሞ በልዩ ሁኔታ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች መብትና ጥቅም ከማስከበር በተጨማሪ የአገራችንን ዴሞክራሲ ለማጐልበት የተለየ እንቅስቃሴ ይደረጋል፡፡ ከዚህ አኳያ አንዱ ቀዳሚ ስራ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በሚደረግ ድርድር የምርጫ ህጋችንን የማሻሻል ጉዳይ ይሆናል፡፡ አገራችን የምትመራበት የምርጫ ህግ በብዙ አገሮች እንዳለ የሚሰራበት ቢሆንም፣ ከእኛ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድምፅ ሊሰማ የሚችልበትን አስተማማኝ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ ከመገኘቱ ጋር የህግ ማሻሻያ ይደረጋል፡፡ ስለሆነም የምርጫ ህጋችን የአብላጫ ድምፅና የተመጣጣኝ ውክልና ስርዓቶችን በትክክለኛ ሚዛን ያጣመረና የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድምፅ የሚሰማባቸው ምክር ቤቶች እንዲኖሩን ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ እንዲስተካከል ይደረጋል፡፡ ይህም በፓርቲዎች መካከል በሚካሄድ የሰጥቶ መቀበል መርህ የሚገዛና አገራዊ ጥቅማችንን ማዕከል ባደረገ ግልፅነትን የተላበሰ የድርድር ሂደት የሚፈፀም ይሆናል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ዴሞክራሲያችንን ከማስፋት አኳያ በሁሉም ደረጃዎች የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ትርጉም ያለውና ውጤታማ ተሳትፎ የሚያደርጉበት ስርዓት እንዲዘረጋ ይደረጋል፡፡ በዚህ ረገድ ከከፍተኛ ጀምሮ እስከዝቅተኛው እርከን ድረስ የሚገኙ የመንግስት ኃላፊዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚኖራቸው ተሳትፏዊ መስተጋብር ህግና ስርዓት እንዲበጅለትና ተጠያቂነትን በሚያረጋግጥ አግባብ እንዲፈፀም ይደረጋል፡፡ መንግስት በዚህ ረገድ ያለው አፈፃፀም በቀጣይነት ለባለድርሻ አካላት እየቀረበ የሚገመገምበትና ተፈላጊ የማስተካከያ እርምጃዎች የሚወሰዱበት ስርዓት በስራ ላይ እንዲውል ይደረጋል፡፡
የዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን በሚደነግገው መሰረት በሁሉም ክልሎች ከማንነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች በተቻለው ፍጥነት የተሟላ እልባት እንዲሰጣቸው ይደረጋል፡፡ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የአስተዳደር አካላት በየክልላቸው የሚገኙ እውቅና ያልተሰጣቸው ማህበረሰቦች ጉዳይ እስካሁንም መቆየት ያልነበረበት ስህተት እንደሆነ በመገንዘብ፣ ይህንኑ በአፋጣኝና በማያዳግም ሁኔታ እንዲያስተካክሉ ይደረጋል፡፡ ማህበረሰቦቹም ይህን አጋጣሚ ለእኩልነት እንጅ ለበላይነት በማይበጅ አቅጣጫ የማይጠቀሙበት እንደሆነ ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ማንኛውም ለበላይነት የሚደረግ እንቅስቃሴ እውቅናን ከመከልከል የማይተናነስ ስህተት እንደሆነ በመገንዘብ፣ መብትን በትክክለኛው ደረጃና መጠን ለማስከበር ብቻ ተግተው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የአስፈፃሚውን አካል ሥራዎች ውጤታማ ለማድረግየሚያከናውናቸውን የቁጥጥር ሥራ መልካም ጅምሮች የበለጠ ከማጐልበት በተጨማሪ የተያያዝነውን የዕድገትና ትራንፎርሜሽን ጉዞ ለማሳካት የሚያግዙ አዋጆችን እንደሚያወጣ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ አኳያ በዘንድሮ ዓመት የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመደንገግ የሚወጣውን አዋጅ ጨምሮ ሌሎች በርካታ አዋጆች የሚወጡ ይሆናል፡፡
የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣
የተከበራችሁ መላ የአገራችን ህዝቦች፣
መንግስት በነደፈው መሰረታዊ የለውጥ አቅጣጫ እየተመራ ላለፈው ሩብ ምእተ ዓመት አገራችንን ከማሽቆልቆል አውጥቶ በእድገት ጐዳና እንዳረማመዳት ከመላ ህዝባችን የተሰወረ አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ ባለፉት አሰራ አምስት ዓመታት በዓለም ፈጣን የሚባለውን እድገት በማስመዝገብ ስንጓዝ መቆየታችን አያከራክርም፡፡ ከዚህ መሰረታዊ ስኬት በመነሳት መላ የአገራችን ህዝቦች በሁሉም መስክ የተጀማመሩ መልካም ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ልባዊ ፍላጐት እንዳላቸው መንግስት በጥብቅ ይገነዘባል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አገራችንን ወደ ፊት ባራመድንባቸው በእነዚህ ዓመታት፣ በተለይ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ችግሮች እንዳገጠሙን ይታወቃል፡፡ እነዚህ ችግሮች በአንድ በኩል ከፍ ሲል እንደተገለፀው ከእድገታችን ጋር ተያይዘው የመጡ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በየደረጃው በሚገኙ የመንግስት አመራር አካላት ዘንድ በሚታዩ የአቅም ማነስ ድክመቶች፣ በተለይ ደግሞ በስነ ምግባርና ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት የማገልገል ጉድለቶች ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮች ናቸው፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግሮችም ሆነ የህዝባችንን ተጠቃሚነት በተገቢው ደረጃ ያለማረጋገጥ ድክመት ከእነዚህ የሚመነጩ ናቸው፡፡ በመንግስት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የተቀመጡ ሰዎች የተረከቡትን ህዝባዊ አደራ በመዘንጋት፣ ስልጣንን የግል መጠቀሚያ የማድረግ አተያይና በዚህም ላይ የተመሰረተ ተጨባጭ ስህተት ከመፈፀማቸው ጋር ተያይዞ የተከሰተ ውጤት ነው፡፡ ይህ በጉልህ መታየት በጀመረበት ጊዜ ሁሉ የእድገታችን ፍጥነት መቀነሱም ሆነ የህዝብ ተጠቃሚነት ለአደጋ መጋለጡ አይቀርም፡፡
መላ የአገራችን ህዝቦች በየአካባቢው ሲመለከቱት የቆየውን ምግባረ ብልሹነትና በስልጣን ካላግባብ የመጠቀም ዝንባሌ መነሻ በማድረግ ቅሬታቸውንና የሚታያቸውን የመፍትሄ ሃሳብ እያቀረቡ ሲታገሉ ቆይተዋል፡፡ እነሆ ይህን የህዝብ ትግል መነሻ በማድረግና ከልብ በመቀበል መንግስት ባሳለፍነው ዓመት መጨረሻ ራሱን ከዚህ ዝንባሌ ለማፅዳት ቁርጠኛ እንቅስቃሴ ማካሄድ ጀምሯል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ቀደም ሲል የተጀመረውን አገራዊ ህዳሴ ከመቀዛቀዝ አውጥቶ ወደ ቀጣይ የለውጥ ሂደት ለማሸጋገር አንዱ ቁልፍ እርምጃ መንግስታዊ ስልጣንን ወደግል መሳሪያነት ለማሸጋገር የሚደረገውን ይህን ዝንባሌና ጥረት በማስቆም፣ መንግስት በርግጥም የህዝብና የአገር መገልገያ መሳሪያ መሆኑን ማረጋገጥ ነው፡፡
ከዚህ በመነሳት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስራውን በሚጀምርበት በሚቀጥለው ወር የፌዴራል መንግስትን በአዲስ መልክና ቅኝት ለማዋቀር ተግባራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ይደረጋል፡፡ በዚህ መሰረት የመንግስት ስልጣንን ካላግባብ የመጠቀም ዝንባሌን የሚገታና ከእንግዲህ በውጤት አልባነት የመንግስት ስልጣን ላይ ተቀምጦ መቆየት የማይቻል መሆኑን የሚያረጋግጥ አዲስ የመንግስት ምክር ቤት የማደራጀት እንቅስቃሴ ይካሄዳል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ የተቻለውን ያክል ብቃትና ቅንነት ያላቸውን ግለሰቦች በኃላፊነት ላይ በማስቀመጥ፣ የመንግስት የስራ አፈፃፀም በውጤትና በውጤት ብቻ የሚመራ እንዲሆን ማድረግ ይጀመራል፡፡ ይህን ተከትሎ ውጤት ያላመጣ ማንኛውም ሰው በማንኛውም ሽፋን በመንግስት ስልጣን ላይ እንደማይቀጥል የሚያረጋግጥ ቋሚ የአሰራር ስርዓት ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል፡፡
የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣
የተከበራችሁ መላ የአገራችን ህዝቦች፣
ለማንም ግልፅ እንደሚሆነው አገራችን የምትገኝበት የእድገት ደረጃ ከጥልቅ ድህነት ለመውጣት የሚደረግ መፍጨርጨር ያለበት እና በየጊዜው ውስብስብ ሁኔታዎች  የሚከሰቱበት መሆኑ የማያጠያይቅ ቢሆንም ላለፉት 25 ዓመታት እንደተመለከትነው በሁሉም መስፈርቶች ወደፊት ስንራመድ ቆይተናል፡፡ በኢኮኖሚና ማህበራዊ፣ በዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር እንዲሁም በውስጣዊ ሰላምና አለም አቀፍ ግንኙነት መስክ ረጅም ርቀት ተጉዘናል፡፡ በመሆኑም በዚህ መድረክ ከተከሰቱት አጠቃላይ ሁኔታዎች በመነሳት በመላ የአገራችን ህዝቦች ትግልና ጥረት የተመዘገቡ ድሎችን በማስጠበቅ፣  መልካም ጅምሮችን ዳር በማድረስና የህዝባችንን ተጠቃሚነት በማስፋት ማሳካት  ይገባናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እድገታችን የወለዳቸው አዳዲስ ተግዳሮቶችን ጨምሮ ከራሳችን የአመራር ድክመት የፈለቁና በአገራችን ፊት የተደቀኑ ችግሮች ደግሞ አስተማማኝ መፍትሔ የሚሹ ሆነው የሚገኙ ናቸው፡፡ እነዚህን ተግዳሮቶች በፈርጅ በፈርጃቸው እየፈቱ መልካሙን ጅምር አጠናክሮ ለማስቀጠል፣ በሁሉም መስክ ሚዛኑ የተጠበቀና ህገ መንግስታዊ ስርዓታችንን በተከተለ አኳኋን የሚካሄድ ትግልን ማጠናከር የግድ ይላል፡፡ ሰላማችንን ለማወክ የሚሹ የውስጥና የውጭ ፀረ-ሰላምና አሸባሪ ሃይሎችን በአስተማማኝ ሁኔታ እየመከትን ነገር ግን ደግሞ ተግዳሮቶችና ችግሮችን በአስተማማኝ ደረጃ ለመፍታት የሚያስችል በህገ-መንግስታዊ መርሆዎቻችን በመመራትና በዚሁም በመገዛት የሚካሄደውን ትግል ማጠናከር ይገባናል፡፡
አገራችን በጠንካራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ መሰረት ላይ በተገነባችበት በዚህ ወቅት ህገ-መንግስታዊ ስርዓታችንን አስተማማኝ የለውጥ መሳሪያ አድርገን እስከተጠቀምንበት ድረስ በርግጥም ረጅም በማይባል ጊዜ ያሰብነውን ግብ ማሳካት እንደምንችል እምነቴ የፀና ነው፡፡
 አመሰግናለሁ
Spokesperson's Directorate General

Spokesperson's Directorate General of the Ministry of Foreign Affairs of the Federal Democratic Republic of Ethiopia.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *